"በእኔ በኩል ቀጣዩ ሕይወቴ አውስትራሊያ ይሁን ኢትዮጵያ አላውቅም" ዳይሬክተር ዐቢይ አየለ

Abiy Aust Eth.png

Theatre and Film Director Abiy Ayele. Credit: SBS Amharic

Get the SBS Audio app

Other ways to listen

በአንድ የጀርመን ባለስልጣን "ሰርከስ ኢትዮጵያ ጀርመን ውስጥ ኮካ ኮላ የሚታወቀውን ያህል በልጆች ዘንድ ይታወቃል" የተባለለት ድርጅት ዳይሬክተር የነበረው ዐቢይ አየለ፤ ስለ ጥገኝነት ጥየቃ ውጣ ውረዶችና የአውስትራሊያ ሕይወት ጉዞ ጅማሮው ይናገራል።


አውስትራሊያ

ዐቢይ ከሀገር ቤት ከመነሳቱ በፊት ዕሳቤው የነበረው በለስ ከቀናው ኑሮውን ጀርመን ወይም አውስትራሊያ ለማድረግ ነበር።

ከቶውንም የጥገኝነት ጥየቃ ሂደቱ ሁለት ዓመታት እንኳ ቢፈጅበት፤ የጎዳና ትዕይንት እያሳየ፤ ጎዳና እያደረ ለመቆየት የወሰነ ቁርጠኛ መንፈስ ነበረው።

እሱን ጨምሮ 30 ሆነው ከወጡት የሰርከስ ኢትዮጵያ አባላት ውስጥ 15ቱ አውስትራሊያ - ሜልበርን ከተማ ቀሩ።

በጋራ መኖር፤ የሰርከስና የሙዚቃ ሙያቸውን በአዲስ አገር፣ በብርቱ የጥገኝነት መንፈስ ጀመሩ።

ትዕይንታቸው ከልምምድ ወደ መድረክ አመራ።

የጥገኝነት ጥየቃቸው ለስኬት እንዲበቃ በእጅጉ ከደከመላቸው በቪክቶሪያ የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ማኅበር የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት የዕንቁጣጣሽ መድረክ አንስተው፤ በተለያዩ የአውስትራሊያ ክፍለ አገራት መድረኮች ላይ መድመቅ ያዙ።

የግል ሕይወታቸውን መምራት ጀመሩ።
ሰርከስ ኢትዮጵያ ጀርመን ውስጥ ኮካ ኮላ የሚታወቀውን ያህል በልጆች ዘንድ ይታወቃል።
አንድ የጀርመን ኢሚግሬሽን ባለ ስልጣን
ኑሮ በአውስትራሊያ

ከአንድ ዓመት ከመንፈቅ ብዙ ውጣ ውረዶች በኋላ የመኖሪያ ፈቃዳቸውን ያገኙት የሰርከስ ኢትዮጵያ አባላት ትኩረት የእፎይታና አዲስ ሕይወት ግንባታ ላይ አረፈ።

እህል ውኃቸው አውስትራሊያ ሆነ።

ዐቢይ እራሱን ለመደጎም በፋብሪካና የታክሲ ሥራ ተሠማራ።

የሥነ ልቦና ትምህርትም ጀመረ።

ሆኖም በግማሽ ቀን ሥራ ገቢ እራሱንና የሀገር ቤት ቤተሰቡን መደጎም አለመቻል ብርቱ ሳንካ ሆነበት።

የአንደኛ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን አቋረጠ።

አጫጭር ኮርሶችን እየወሰደ ክህሎቱን ማጎልበቱን ቀጠለ።

በፊልም ሥራ ሙያው እየገፋ ሔደ።

ልብ ወለድና ዘጋቢ ፊልሞች

የዐቢይ የፊልም ሥራ መነሻ አውስትራሊያ ሳይሆን ኢትዮጵያ ነው።

"የወንዶች ጉዳይ"፣ "522" እና "ኮሞሮስ" ፊልሞችን ከሙያ ባልደረባዎቹ ጋር ሆኖ ሠርቷል።

ከአውስትራሊያ ወደ ሀገር ቤት በመመለስ በዳይሬክተርነት የመራውን "ፊደል አዳኝ" የፊልም ሥራ ለሕዝብ አቀረበ።

በኢትዮጵያና አውስትራሊያ ታዳሚዎች ዘንድ ትልቅ አድናቆትን አተረፈለት፤ ለስኬት በቃ።

ኢትዮጵያ ውስጥ ሙሉ በሙሉ በፊልም ኢንዱስትሪ ተሠማርቶ ጠቅልሎ ለመኖር ወጠነ። ትልሙ ሳይሰምር ቀረ።

ወደ አውስትራሊያ ተመለሰ።

ነዋሪነታቸው ሜልበርን ከተማ ነዋሪውንና የመብራት ኃይል ስፖርት ክለብ መሥራቹን አንጋፋ የስፖርት ሰው የአቶ ወንድሙን ግለ ታሪክ በዘጋቢ ፊልም ሠርቶ ለሕዝብ አቀረበ።

በታዳሚዎች ዘንድ 'ግሩም ሥራ' ተባለለት።

በእዚያ ተወስኖ አልቀረም፤ ከአንድ ወር በፊት "የኤልያስ ዋንጫ" በሚል ስያሜ የዝነኛውን የመብራት ኃይልና የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ተጫዋች ኤልያስ ጁሐርን ግለ ታሪክ በዳይሬክተርነት መርቶ፤ በዘጋቢ ፊልም ቀርፆ አቀረበ።

"ድንቅ" ተሰኘ።

የዐቢይ የጥበብ ሥራዎች አውስትራሊያ ውስጥ በልብ ወለድና የግለ ታሪክ ዘጋቢ ፊልሞች ብቻ የተወሰኑ አይደሉም።

ቀደም ሲል፤ በቲአትር ዘርፍ የኢትዮጵያውያን - አውስትራሊያውያንን ሕይወት ያንፀባረቀ "ምስቅልቅል" የተሰኘ ተውኔት ደርሶ ለመድረክ አቅርቧል።

ቲአትር ለዐቢይ የሕይወት ፍቺ ማግኛ ቢሆንም፤ ወደ ቲአትሩ ዓለም ተመልሶ ለመዝለቅ እንዳይችል ግድ የሚሉት ሳንካዎች እንዳሉ ያነሳል።

መቼና እንዴት ለሚለው አሁነኛ ምላሽ ባይኖረውም፤ ከፊልም ሥራው ጋር ግና እንደማይለያዩ ፅኑ አመኔታ አለው።

የእራሱን ግለ ታሪክም ፅፎ ከመቋጫው ገሚስ ላይ አድርሷል።

ስኬትና ተግዳሮት

በአውስትራሊያ ሕይወቱ የመጀመሪያዎቹ አምስት ዓመታት ለብርቱ የመንፈስ መታወክ እስከመዳረግ የደረሰ ቢሆንም፤ ለሜልበርንና አዲስ አበባ ያለው ፍቅር ግና የጋለና ነፋስ የማይገባው ነው።

አውስትራሊያ በርካታ ስኬቶችን አላብሳዋለች።

የወደፊት ሕይወቱ መገባደጃና የዕፎይታ ዘመኑን ማሳለፊያ ኢትዮጵያ ትሁን አውስትራሊያ እርግጠኛ አይደለም።




Share