መለስ ሳህሌ፤ ከድሬዳዋ እስከ አውስትራሊያ

Meles Sahle.png

Meles Sahle, former Executive Producer of SBS Amharic Service. Credit: SBS Amharic

Get the SBS Audio app

Other ways to listen

የቀድሞው የSBS አማርኛ አገልግሎት ዋና አዘጋጅ መለስ ሳህሌ፤ ስለ ድሬዳዋ ትውልድና ዕድገቱ፣ የጂቡቲ ስደት ፈተናዎቹና የአውስትራሊያ የሠፈራ ሕይወቱ ያወጋል።


ውልደትና ዕድገት

መለስ ሳህሌ፤ ትውልድና ዕድገቱ በአዲስ ከተማ - ድሬዳዋ ነው።

ከቄስ ትምህርት ቤት ሀ ሁ ቆጠራ አንስቶ የሁለተኛ ደረጃ የቀለም ትምህርቱን ያጠናቀቀውም እዚያው ድሬዳዋ ከተማ ነው።
Sahle.png
Credit: M.Sahle

ከድሬዳዋ ትውስታዎቹ መካከል ዛሬም ድረስ ጎልቶ የሚታየው በነዋሪዎቹ ዘንድ በዘር፣ በሃይማኖትና መጤነት ላይ ያልቆመ፤ ሕብረ-ብሔራዊ ትስስብና ፍቅር የተመላበት ሕብረተሰባዊ ዕሴት ነው።
በእርግጥም 'ድሬዳዋ የፍቅር ሀገር ናት' የሚባለው እውነት ነው፤ ከሌላ አካባቢ በጣም የተለየች ናት።
መለስ ሳህሌ
ድሬዳዋ በመለስ የወጣትነት ዘመን እንደ ሌሎች የኢትዮጵያ ክፍለ አገራት ሁሉ የ1966ቱ የኢትዮጵያ አብዮት ዋነኛ አካል የሆነው የተማሪዎች ንቅናቄ ተካሂዶባታል።

ሶሻሊስታዊ ርዕዮተ ዓለም ተቀጣጥለውባታል። ለአብዮቱ የቆሙ ወጣቶች፤ በአብዮቱ ወድቀውባታል። ዘብጥያም ወርደውባታል።
Supporters.png
Images of the founders of "scientific socialism" (from left) are Karl Marx, Friedrich Engels, and the Russian Bolshevik revolutionary leader Vladimir Ilyich Lenin at Revolution Square in Addis Ababa on September 13, 1987. Credit: ALEXANDER JOE/AFP via Getty Images
ወቅቱ የመጨረሻው የኢትዮጵያ ሰለሞናዊ ሥርዓትና የንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ አገዛዝ ያከተመበት፤ ሶሻሊስታዊ ሥርዓትን ለማቆም ርዕዮተ ዓለሙን የማዕዘን ደንጊያቸው ያደረጉ ግራ ክንፈኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የፈሩበት ነበር።

ከፓርቲዎቹ አንዱ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮት ፓርቲ (ኢሕአፓ) የአያሌ ወጣቶችን ቀልብ በአብላጫ ሳበ።
EPRP.png
Logo of Ethiopian People's Revolutionary Party. Credit: WikiImage
መለስም በኢሕአፓ የወጣቶች ሊግ አባልነት ተርታ ቆመ።

አብዮቱ እጅግ በፈጠነ ሂደት መገስገስ ያዘ። ወደ ብሔራዊ የፖለቲካ መድረክ መውጣት የጀመሩት ፓርቲዎች አዘገሙ። የፖለቲካ ስልጣን ዙፋኑን ከብቦ በያዘው የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊት እጅ ገባ።

ኢትዮጵያ በጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ መመራት ጀመረች።
Derg.png
Mengistu Haile Mariam (3rd-L), Ethiopian leader and chairman of the Provisional Military Administration Council (1977-87) and future Ethiopian President (1987-91), Ethiopian General Teferi Bante (C), Chairman of the Military Council, and Ethiopian revolutionary leader Atnafu Abate review a military and students' parade on 29 December 1974 in Addis Ababa. Credit: J. M. BLIN/AFP via Getty Images
በደርግና የፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ የስልጣን ጥያቄ ምላሾችና ርዕዮተ ዓለማዊ አተያዮች በክብ ጠረጴዛ ለመታደም እምቢኝ አሉ።

የደርግ "ያለ ምንም ድል - ኢትዮጵያ ትቅደም" ሀገራዊ ርዕይ ወደ "ነጭ" እና "ቀይ" ሽብር ተለወጠ።

የአያሌ ኢትዮጵያውያን ሕይወቶች ተቀጠፉ። ዘብጥያዎች በፖለቲካ እሥረኞች ተጨናነቁ።

ከታሳሪዎችም አንዱ መለስ ሳህሌ ነበር። ለአንድ ዓመት ሐረር እሥር ቤት ቆይቶ ወጣ።

ወደ ድሬዳዋ ተመለሰ።

ድሬዳዋ ግና ዕቅፍ አበባ ይዛ አልጠበቀችውም። ከቶውንም ሳቢያን ዘብጥያ ወረደ።

ለሁለት ወራት ታስሮ ተለቀቀ።

የሐረርና ድሬዳዋ እሥራቶች መለስን ከድንበር ባሻገር እንዲያማትር ግድ አሉት።

ስደት ዕጣ ፈንታው ሆነ።

ጂቡቲ

መለስ በእግር ተጉዞ ጂቡቲ ገባ።

ጁቡቲ በስደት ተግዳሮት ፈተነችው።

የዕለት ጉርስ፣ የዓመት ልብስና መጠለያ ፈጥና አልቸር አለችው።

ይሁን'ጂ ለዘጠኝ ዓመታት የጂቡቲን የስደት ሕይወት ተቋቋመ፤ ሲልም ውቅያኖስን በጢያራ አቋርጦ ለዳግም ሠፈራ በቃ።

አውስትራሊያ

የጂቡቲ የስደት ፈተናዎች ሰብዕናን በተላበሰው ማለፊያ የአውስትራሊያ አዲስ የሕይወት ምዕራፍ ተተኩ።

ሆኖም፤ መለስ የአውስትራሊያን መሬት በረገጠበት ወቅት እንደ አሁኑ ቁጥራቸው የበዛ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያኖች አልነበሩም።

የብቸኝነት ስሜት ያድርበት ጀመር።

ለዘጠኝ ዓመታት ስደትን የተቋቋመው መንፈስ ግና በሠፈራ ሕይወት ተግዳሮቶች እምብዛም አልታወከም።

ኑሮ መልኩን ቀይሮ ቀጠለ።

ከግል ሕይወት ዐልፎም ማኅበረሰብን የማገልገል ዕድል ይዞ መጣ።

በማኅበረሰብ ራዲዮ ጣቢያ አገልግሎት የተሟሸ የጋዘጠኛነት ሙያ፤ መለስን በአውስትራሊያ መንግሥት ለሚተዳደረው የሕዝብ ብዙኅን መገናኛ የSBS አማርኛ አገልግሎት ዋና አዘጋጅነት አበቃው።

የፕሮፌሽናል ጋዜጠኛነት ስልጠና ተሰጠው። የSBS አማርኛ አገልግሎት ስርጭቱን በመለስ አንደበት በወርኃ ኖቬምበር 2003 በመላ ሀገረ አውስትራሊያ ማስተጋባት ጀመረ።

በግል ጉዳይ ሳቢያ የSBS አማርኛ አገልግሎትን ፈቅዶ እስከለቀቀ ድረስ ለአምስት ዓመታት በዋና አዘጋጅነት ሙያዊ አገልግሎቱን አበረከተ።

ከስቱዲዮ ተሰናበተ።

በSBS አማርኛ አገልግሎት ዘንድ ግና ታሳቢነቱ ዘላቂ ሆኖ አለ።






Share