ዶ/ር ብሩክ ይርሳው፤ ከድሬዳዋ እስከ አውስትራሊያ

Biruck pic 1.jpg

Dr Biruck Yirsaw. Credit: B.Yirsaw

Get the SBS Audio app

Other ways to listen

ዶ/ር ብሩክ ይርሳው፤ እንደምን ከአገረ ኢትዮጵያ በጃፓን ዞረው ለአውስትራሊያ ምድር እንደበቁ፤ የትምህርት፣ የሥራ፣ የቤተሰብ፣ ማኅበረሰባዊና መንፈሳዊ ሕይወት ትስስሮሻቸውን አንስተው ያወጋሉ።


አንኳሮች
  • ውልደትና ዕድገት
  • ትምህርትና የሥራ ዓለም
  • ሠፈራ
ውልደት፣ ዕድገትና ትምህርት

የዶ/ር ብሩክ ይርሳው ውልደትና ዕድገት መብራት ኃይል ቀበሌ - ድሬዳዋ ነው።

ከአንደኛ እስከ ሁለተኛ መለስተኛ ደረጃ ያለውን የስምንት ዓመታት የቀለም ጉዞ ያጠናቀቁት በከዚራ / ሚካኤል ትምህርት ሲሆን፤ ቀሪውን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የፈፀሙት በድሬዳዋ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው።

ለጥቀው፤ በቀድሞ አጠራሩ የጅማ ጤና ኢንስቲትዩት፤ በአሁነኛ መጠሪያው የጅማ ዩኒቨርሲቲ ዘልቀው በአካባቢ ጤና ሙያ ተክነው ተመረቁ።

ለጤና መስክ ሥራ ስንዱ ሆኑ።

የሥራ ዓለም

የመጀመሪያ ሙያዊ አገልግሎታቸውን በኢትዮጵያና ሶማሊያ ድንበርተኛ በሆነች አንዲት የኢትዮጵያ ሶማሌ ክፍለ አገር ዞን በለጋ ዕድሜያቸው ጀመሩ።
Biruck Somali.jpg
Biruck Yirsaw in the Ethiopia-Somalia border town. Credit: B.Yirsaw
ለሶስት ዓመታት መሰናክሎችን እያለፉ፤ የአካባቢ ጤና ባለሙያ አገልግሎታቸውን በቅንነት አበረከቱ።

ከዚያም በደቡብ ዩኒቨርሲቲ - በአሁኑ አጠራር ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በረዳት መምህርነት ተሠማሩ።

ሲልም፤ በጥናት መስክ የምርምር አስተዋፅዖዎችን ለሁለት ዓመታት ከሌሎች ተመራማሪዎች ጋር በትብብር ሲያካሒዱ ቆዩ።

በእዚያም አልተወሰኑም፤ ክህሎታቸውን ለማላቅ ወሰኑ።

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተው በአካባቢ ሳይንስ ትምህርት በሁለተኛ ዲግሪ ተመረቁ።

የቀሰሙት ከፍ ያለ ዕውቀት ዕሴት ሆናቸው። በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ለአካባቢ ጤና ትምህርት ኃላፊነት፣ የአስተዳደር፣ የሴኔት አባልነትና የልዩ ግብረ ኃይል መሪነት አበቃቸው።

ይሁንና የሕይወት ጥሪ ተልዕኳቸው በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲና አገረ ኢትዮጵያ ተወስኖ አልቀረም።

ወደ ሩቅ ምሥራቅ ወሰዳቸው።

ከአገር ቤት ወደ ባሕር ማዶ

አቶ ብሩክ በትምህርት ሚኒስቴር አማካይነት ወደ ሕንድ አቅንተው እንዲማሩ የነፃ ትምህርት ዕድል አገኙ።

ሆኖም፤ ከጃፓን መንግሥት ለአምስት ዓመታት የምርምር ዘርፍ ነፃ የትምህርት ዕድል በማግኘታቸው ወደ ኪዮቶ ዩኒቨርሲቲ አቀኑ።
Biruck Japan.jpg
Field Research. Credit: B.Yirsaw
ለሁለት ዓመታትም በኪዮቶ ዩኒቨርሲቲ የምርምር መስክ ተሠማርተው ቆዩ።

የቤተሰብ፣ የቋንቋና ባሕል ዝንቅ ድምሮች አስባብ ሆነው ቀልባቸው አውስትራሊያ ላይ አረፈ።

በደቡብ አውስትራሊያ ዩኒቨርሲቲ ሶስተኛ ዲግሪያቸውን እንዲከውኑ ነፃ የትምህርት ዕድል አገኙ።

ጓዛቸውን ሸክፈው ከእነ ቤተሰባቸው የአውስትራሊያን ምድር ረገጡ።

በሶስት ዓመት ተኩል የምርምር ጥናታቸውን አጠናቅቀው ተመረቁ።
Graduation.jpg
Graduation. Credit: B.Yirsaw
በአካባቢ ሳይንስ የምርምር ውጤታቸው ግኝትም የSBS ሬዲዮ አማርኛ ፕሮግራምን ጨምሮ በዋነኛ የአውስትራሊያ ብዙኅን መገናኛ ሽፋንን አስገኘላቸው።
በአሁኑ ወቅት በዊንድሃም ክፍለ ከተማ የአካባቢ ጤና ሙያ አገልግሎት ላይ ተሠማርተው ያሉ ሲሆን፤ ጎን ለጎንም የምርምር ሥራቸው እያካሔዱ ይገኛሉ።

በታካይነትም ማኅበረሰባዊ ተሳትፎዎችንና መንፈሳዊ አገልግሎቶችን እያበረከቱ አሉ።
Biruck community sport.jpg
Community sport. Credit: B.Yirsaw



Share